27 Apr 2024
የተሻሻለ የድህረ ትራፊክ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ የሙከራ ፕሮጀክት በተመረጡ የመንገድ ኮሪደሮች ላይ የማስጀመሪያ ወርክሾኘ ተካሄደ
የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ከNTU International (ኤን.ቲ.ዩ ኢንተርናሽናል) ከተባለ አማካሪ ጋር በመተባበር የሚተገበረውን የተሻሻለ የድህረ ትራፊክ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ስርዓትን ለማሻሻል እንደሚረዳ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት የትራፊክ አደጋ በተደጋጋሚ በሚደርስባቸው ኮሪደሮች ላይ በሙከራ ደረጃ ለመተግበር እንዲቻል ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የምክክር ወርክሾኘ ተካሂዷል፡፡

የዕለቱን ወርክሾፕ ያስጀመሩት የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አባሶ ሲሆኑ በንግግራቸውም ሙከራው የሚጀመርባቸው በአራት የመንገድ ኮሪደሮች ማለትም ከአዲስ አበባ-ፍቼ፣ ከአዲስ አበባ - አዳማ የፍጥነት መንገድ፣ ከባህርዳር - እንጅባራ እና ከሆሳና- ቡታጅራ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህንን ኘሮጀክት የሙከራ አፈፃፀም ስኬታማ በሆነ መንገድ ለማሳካት የትራፊክ ፖሊስ፣ የህክምና፣ የትራስፖርት ቢሮዎች እና የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን በመወጣት የሙከራ ትግበራውን በስኬት በማጠናቀቅ በቀጣይ የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባቸውን አካባቢዎችን ተደራሽ ለማድረግና የተሻሻለውን የድህረ ትራፊክ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት ለማሻሻል አስተዋፆ ከፍተኛ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡ አክለውም በተመረጡት ኮሪደሮች ላይ የድህረ ትራፊክ አደጋ ምላሽ አሰጣጡ በአለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት በተቀናጀ መንገድ ፖሊስ እና የመጀመርያ እርዳታ ሰጪ የህክምና ባለሙያዎች አደጋው በተከሰተበት ቦታ ከአንድ ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በመገኘት ክቡሩን የሰው ህይወት እንዲታደጉ እንዲሁም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል የሚያስችል መሆኑንና፤ ለዚህም አገልግሎት የሚውሉ በቂ ግብዓቶች እና የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶች እንደሚሟሉ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡ የሙከራ ትግበራው ዓላማ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት እ.ኤ.አ ከ2023-2030 ድረስ በግማሽ ለመቀነስ የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ከያዘው ዕቅድ ጋር የተናበበ መሆኑን የአማካሪው ባለሞያዎች ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በመርሐ ግብሩ ላይ ኮሪደሮቹን ለመለየት ጥናት መደረጉ፣ የኘሮጀክቱን ዓላማ እና የሚጠበቀውን ውጤት ተገልጿል፡፡ በፕሮጀክቱ አራት ዋና ዋና ተግባራት ሲኖሩ እዚህም የተሸሻሉ የትራፊክ ህግ ማስከበር ስርዓት፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች፣ የክትትል እና ቁጥጥር ስራዎች እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የድህረ ትራፊክ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ስራዎች እንደሚሰሩ ተነግሯል፡፡ በመጨረሻም በተመረጡት ኮሪደሮች ላይ የተደረጉ የጥናት ውጤቶች እና መርሀ-ግብሩን በጊዜው ለማስጀመር በተመረጡት አካባቢዎች ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት በማድረግ ስራውን በፍጥነት ለመጀመርና እንዲሁም ለኘሮጀክቱ መሳካት የሚረዳ ስትሪንግ ኮሚቴ ከፌደራል እስከ ክልል ተቋማት ውስጥ የማቋቋም አስፈላጊነት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡